በካፋ ዞን በመኸር እርሻ ከ92 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት መልማቱ ተገለጸ

ጥቅምት 9/2014 (ዋልታ) በካፋ ዞን በመኸር እርሻ 92 ሺሕ 706 ሄክታር መሬት መልማቱ ተገለጸ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በላይ ተሰማ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በመጠቀም ከ5ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አተር፣ ባቄላ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና የተለያዩ ሰብሎችን በኩታ ገጠም እርሻ በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ዞኑ አንድ ሺሕ 325 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ያለማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 420 ያህሉ በኩታ ገጠም እርሻ የለማ ነው ተብሏል፡፡

“የማይታረስ መሬት መኖር የለበትም” በሚል መርህ ከእያንዳንዱ አርሶአደር እና ባለሀብት ጓሮ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር በሀገር ኢኮኖሚ እድገትም አስተዋጽኦ ለማበርከት በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዞኑ ከ183 ሺሕ በላይ የጓሮ ቡና ያለማ ሲሆን፣ 50 ሚሊየን ያህል የቡና ችግኝ መትከል ችሏል።

በቀጣይም የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አዲስ የተመሰረተውን የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ መስህቦችን የታደለ በመሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ባለሀብቶች በዞኑ እና በዙሪያው አካባቢዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በሔለን ታደሰ