በክልሉ ለሚገኙ 71 ሺሕ ተፈናቃዮች ድጋፍ መደረጉን ኮሚሽኑ አስታወቀ

ደበበ ዘውዴ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ለሚገኙ 71 ሺሕ ተፈናቃዮች በመንግሥት፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ እና በአጋር አካላት ቅንጅት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ መደረጉን የአደጋ ሥራጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት በአማራ ክልል ለሚገኙ 71 ሺሕ ተፈናቃዮች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለአንድ ወር ቀለብ የሚያገለግል 10 ሺሕ 603 ኩንታል ምግብ ለተፈናቃዮች እንዲከፋፈል ተደርጓል።

በተጨማሪም 28 ሺሕ 625 ልዩ ልዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ ከኮሚሽኑ ክምችት ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ለመጠለያ ካምፖቹ መሰራጨቱን ገልጸው ኮሚሽኑ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለእነዚሁ ካምፖች ለወጪ እንዲውል ወደ ክልሉ እንዲላክ ማድረጉንም አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከአላማጣ ከተማ፤ ከአላማጣ ዙሪያ ከኮረም፣ ከኦፍላ፣ ራያ ባላ፣ ዛታ እንዲሁም ከራያ ቆቦ ገጠር ቀበሌዎች ተፈናቅለው በራያ ቆቦ ከተማ በተለያዩ አምስት የመጠለያ ጣቢያዎች እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተጠልለው 56 ሺሕ 701 ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዋግ ኸምራ ዞን ፃግብጅና አበርገሌ ወረዳዎች ከሁሉም ቀበሌዎች፣ ከዝቋላ ወረዳ ስድስት ቀበሌዎች፣ ከሰቆጣ ዙሪያ አንድ ቀበሌ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 67 ሺሕ 488 ዜጎች መኖራቸውን አክለዋል። ከዚህ ውስጥ 49 ሺሕ 184 ያህሉ በሰቆጣ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተጠልለው 18 ሺሕ 304 ወገኖች ደግሞ በፅታ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

መንግሥት የሚፈናቀሉ ዜጎችን ለመቀበል ተጨማሪ ካምፖችን እየገነባ መሆኑን እና በዚህም በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ አካባቢ 88 ሺሕ ሰዎች መያዝ የሚችል 400 ሄክታር መሬት ላይ ጊዜያዊ መጠለያ ዝግጁ መደረጉን መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ቆቦ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሀብሩ ላይ መጠለያ በማዘጋጀት ወደዚሁ መጠለያ እንዲገቡ ተደርጎ 16 ሺሕ 211 ወገኖች እስካሁን ወደ ተዘጋጀው ሳይት መግባታቸው ተገልጿል፡፡

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!