በክልሉ በሕዝቡ አስተዋይነት የጸጥታ ችግሮችን መመከት እንደተቻለ ተገለጸ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በሕዝቡ አስተዋይነት እየተፈጠሩ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን መመከት እንደተቻለ ተገለጸ።
የደቡብ ክልል የጸጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ የክልሉ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አስቸኳይ የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ በክልሉ በአንድ አንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝባችን አስተዋይነት ታክሎበት እየተፈጠሩ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን መመከት እንደተቻለም አብራርተዋል።
መላውን ሕዝብ በማሳተፍ የልማት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን የማስቀጠል ሥራ መከናወኑንም አውስተዋል።
በክልሉ ጸረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግር በደራሼ ልዩ ወረዳ በጸጥታ ኃይሎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተካሂዷል።
ቀጣናው ሰላማዊ እንዳይሆን ዜጎች ሰርተው እንዳይለወጡ የታጠቁ ኃይሎች ችግር በመፍጠር ላይ ናቸው ብለዋል። በኮንሶ እና በአሌ አካባቢዎችም የጸጥታ ችግሮች መስተዋላቸውንም አስረድተዋል።
በኮንሶ ደራሼ እና አሌ አካባቢዎችም የጸጥታ ችግር መከሰቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የቡርጂ እና አማሮ አካባቢዎች ጠላት መሽጎ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አብራርተዋል።
የሕዝቡን ሰላም በሚረብሹ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ሲሉም አስረድተዋል።
ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በደራሼ አካባቢ ህግ የማስከበር ሥራ በመሰራቱ ከ450 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 17 አመራሮችና የጸጥታ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን የጸጥታ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ 650 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ጠቁመዋል። ከነዚህ ውስጥ 11 አመራሮችም በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አብራርተዋል።
ጠላት በክልሉ የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት ጥረት ማድረጉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የሃይማኖት ብዝኃነት በሚስተናገድበት ክልል ግጭት በማስነሳት ኅብረተሰቡን ለማሸበር የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በቅርቡ በስልጤ ዞን የተከሰተው ለዚህ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ድርጊቱ የዞኑን ማኅበረሰብ የማይወክል መሆኑን ተናግረዋል።
በግጭቱ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት የኅብረተሰቡን የቆየ መልካም እሴት ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር መሰራት እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት መስጠታቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።