በክልሉ በማዕድን ዘርፍ 200 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ማውጣታቸው ተገለጸ

ኃይሌ አበበ

ጥቅምት 29/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል በማዕድን ዘርፍ 200 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ማውጣታቸው ተገለጸ፡፡

አማራ ክልል የኢንደስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የከበሩ ደንጋዮች፣ የኃይል አቅርቦትና ብረት ነክ በሚባሉ 5 ዘርፎች የተከፈከሉ 40 ዓይነት የማዕድን ባለቤት መሆኑን የክልል ማዕድን ልማት ቢሮ አመልክቷል፡፡

የአማራ ክልል ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ ኃይሌ አበበ ክልሉ በርካታ የማዕድን ባለቤት ቢሆንም ባለፉት ዓመታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ችግር፣ ፖለቲካዊ አሻጥራ እና መሰል ችግሮች ባለው ፀጋ ልክ ሳይጠቀምበት እንዲቆይ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ለዚህ ማሳያው በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ጎጃምና በደቡብ ወሎ ለሲምንቶ ምርት ግብዓት የሚሆኑ ማዕድን እያለ ክልሉ ግን አንድም የሲሚንቶ ፋብሪካ የሌለው ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ እንደ ሀገር ለማዕደን ዘርፉ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ በተሰጠው ትኩረት መሰረት እንደ ክልልም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ዘርፉን የሚመራ አስፈፃሚ አካል በቢሮ ደረጃ በማደራጀት አሰራሮችን በመዘርጋት ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ያለውን የማዕድን ዘርፍ ለአማራ ክልል ብሎም ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዲሰጥ የግል ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በግራናይት፣ በጅብሰን እና በሌሎችም ወደ ምርት እንዲገቡ እየተደረገ ነው፤ የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት እየደገፋቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ እስካሁን ድረስ በማእድን ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ያውጡ ባለሃብቶች  200 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበዋል ያሉት የማዕድን ቢሮ ኃላፊው የአማራ ክልል ባለው የተፈጥሮ ፀጋ ልክ እንዲጠቀም “ማዕድን አዲስ የንጋት ተስፋ ለክልላችን” በሚል በአስር ዓመት ውስጥ 5 የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ 4 የድንጋይ ከሰልና 3 የብረት ፋብሪካዎቸ እንዲኖሩት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት በአንደኛው የሩብ ዓመት 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ፣ 6 ሺሕ ኪሎግራም ኦፓል ደግሞ ለውጭ ገቢያ ማቅረብ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በክልሉ ያለው የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴ ከውጭ የሚገባውን የማዕድን ምርት በሃገር ውሥጥ እንዲተካ፣ የስራ እድል እንዲፈጥር እና የክልሉ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንዲሆን ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

በምንይሉ ደስይበለው