በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ 14 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተቻለ

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ በሁለት ዙር 327 ሺሕ 636 ሔክታር መሬት በማልማት 14 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻሉ ተገለፀ።

በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ በመግለጫቸው እንዳሉት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን በመቋቋም በ2014 በጀት አመት የተያዙ እቅዶችን ማሳካት ችሏል።

በዚህም በክልሉ በሁለት ዙሮች በበጋ መስኖ ስንዴ 327 ሺሕ 636 ሔክታር መሬት በማልማት 14.1 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ በ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አሳይቷል ያሉት የቢሮ ኃላፊ በዚህም ለ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለ አመላክተዋል።

በ2015/16 በጀት የምርት ዘመን በሁለት ዙሮች 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት በመስኖ በማልማት 50 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለማምረት መታቀዱን ነው የገለፁት፡፡

በደረሰ አማረ