በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት የ7 አነስተኛ የመስኖ ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

መጋቢት 4/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት አነስተኛ የመስኖ ተቋማት ግንባታ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

ተቋማቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ 4 ሺሕ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንደሮው ከ380 ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ በግንባታ ላይ ከሚገኙ 8 ነባርና አዲስ የመስኖ ተቋማት ውሰጥ ሰባቱን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ።

ተጠናቀው ለአገልግሎት ከሚበቁት መካከል አችዋ፣ የኢሌይ ኡቾይ፣ የቦንጋ፣ የባሮ ፍንኪዎ፣ የጊሎ ፑቻላ አዲስና ነባር  የመስኖ ተቋማት ናቸው።

ከተቋማቱ መካከል አራቱ በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ቀሪዎቹ በ2007 በዘላቂ የልማት ግቦች ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተቱ የቆዩ መሆናቸው አመልክተዋል።

በዘንድሮው ዓመት በተለይም ግንባታቸው የዘገዩትን ጨምሮ አዲስ የተጀመሩ የመስኖ ተቋማትን በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሰባት ተቋማት የግንባታ አፈፃጸም አበረታች ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተጠናቀው ለማልማት እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል።

ተቋማቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ1 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚያለሙና ከ4 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

የኢሌይ ኡቾይ የመስኖ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ መሪሁን ሻባ በበኩላቸው የመስኖ ተቋሙን ግንባታ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ  አስቀድሞ በማጠናቀቅ ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወሰዱትን የመስኖ ተቋም በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብተው ለማስረከብ በገቡት ውል መሰረት ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የቦንጋ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ብሩክ እንግዳ ናቸው።

በጋምቤላ ክልል የባሮ፣ የጊሎ፣ የአኮቦና፣ የአሌሮ ወንዞችንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ780 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንዳለ ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።