በክልሉ በአምስት ወራት 640 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

በቀለ ተመስገን

ታኅሣሥ 7/2015 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት 640 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ በቀለ ተመስገን የክልሉን የገቢ አፈፃፀምን አስመልተው በሰጡት መግለጫ በክልሉ በ2015 ዓ.ም በአምስት ወራት ውስጥ 627 ሚሊየን ብር ለመሰብስብ ተቅዶ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው 640 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 102.06 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከተሰበሰበው ገቢ 346.6 ሚሊየን ብሩ ከቀጥታ ታክስ፣ 187 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ቀጥታ ካልሆነ ታክስ፣ 40 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም 66 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ142 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ጭማሪ እንዳለው ጠቁመው ይህም የ28.7 በመቶ እድገት ማሳየቱን መናገራቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

በቀጣይም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በማጠናከር በበጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደው 1 ነጥብ 36 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሳካት ይሰራል ብለዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW