በክልሉ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደ ሥራ ተገባ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስና ፓርቲው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ በሰጡት መግለጫ ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫና ውሳኔ መሰረት ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ለመመለስ የአጭርና ረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ በክልል ደረጃ በእቅዱ መሰረት ሥራዎችን እየተከናወኑ እንደሚገኙ በየአራት ቀናት ከአመራሩ ጋር እየገመገመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልሉን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችለውን የ90 ቀን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ከተደረጉ በኋላ ከመጋቢት 29 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ድረስ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑን አመልክተዋል።

በትግበራው ምዕራፍ በፓርቲው የተቀመጡ ግቦችን መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት በሚመለከተው ልክ የራሱን መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምጦ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት ሦስት ወራትም በክልሉ መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ ኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥና ሌብነትን የሚጠየፍ ማኅበረሰብ በመፍጠር ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

ክልሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የጀመረውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆንም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።