ጥቅምት 9/2017 (አዲስ ዋልታ) በሶማሌ ክልል አፍዴር እና ሸበሌ ዞኖች በኩል ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 60 የአልሻባብ የሽብር ቡድን አባላት ላይ እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ የፍርድ ውሳኔ መተላለፉን ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የቡድኑ አባላቱ በ10 የምርመራ መዝገብ ተከሰው እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ የፍርድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተገልጿል።
ፖሊስ በ60 የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ በቂ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃ በማቅረብ በሽብር ወንጀል ምርመራ አጣርቶ ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ተዘዋዋሪ ችሎት ሁለት የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በዕድሜ ልክ እስራት፣ 56 ተከሳሾች እንደወንጀል ተሳትፎአቸው ከ6 ዓመት እስከ 18 ዓመት ፅኑ እስራት እና በአልሸባብ የሽብር ቡድን አባልነት የተከሰሱ ሁለት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው 2 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲፈረድባቸው ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአልሸባብ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር ለመመስረት፤ ከአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ወጣቶችን በመመልመል በሶማሊያ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ ሰላማዊ ሰው መስለው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ መደረጋቸው ተጠቅሷል።
ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው የገቡት አባላቱ ለሽብር ቡድኑ በመሰለል፣ ፈንጂ በማፈንዳት፣ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም አካባቢዎችን የሚቆጣጠር ኃይል ለማዘጋጀት ሲንቀሳቀስ እንደነበር የምርመራ ቡድኑ ባካሄደው ማጣራት ደርሶበታል፡፡
የሽብር ቡድኑ ሐምሌ 11 ቀን 2014 ከሶማሊያ በሰባት ተሸከርካሪና በአራት ሞተር ሳይክል በሌሊት ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሁሉል አካባቢ ሲደርስ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ከአራት ቀን እልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ በርካታ የሽብር ቡድኑን አባላት መደመስሱን የፌደራል ፖሊስ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ሁለት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 92 የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችን በመማረክ 406 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ67 ሳጥን መሰል ጥይቶች፣ 43 ላውንቸር እና 27 ብሬን ከአንድ ሳጥን መሰል ጥይት ጋር እንዲሁም በርካታ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በኤግዚቢትነት መያዛቸውን በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በስድስት የምርመራ መዝገብ 95 ተጠርጣሪዎች በሽብር ወንጀል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።