በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያለመ የፖሊሲ ምክክር ተካሄደ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በክልሎች መካከል ፍትሐዊና ተመጣጣኝ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል የበይነ መንግሥታት ፊሲካል ወይም ወጪና ገቢ ግንኙነት የሚመራበት አሰራርን ለማሻሻል የፖሊሲ ምክክር ተካሄደ።

የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ክልል የሚያከፋፍለውን ሀብት ክትትል ማድረግ የሚያስችል መመሪያ ላይ ውይይት ተደረገ ሲሆን ላለፉት 30 ዓመታት መመሪያው ክፍተት እንደነበረበት ተነስቷል።

በተለይ ከሀብት ክፍፍል ጋር በተያያዘ በሕዝቦች መካከል ግጭትና ቅሬታ እንዲነሳ የሚያደርግ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የፌዴራል መንግሥቱ ለክልሎች የሚሰጠው ድጎማ በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ ሀብት አምጥቷል የሚለው ሊፈተሽ የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ክልሎች የራሳቸውን ወጪ የመሸፈን አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ የክልሎችን አቅም ከማሳደግ አኳያም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለዚህም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በሥራ ላይ ያሉትን ፖሊሲዎች፣ የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች ማሻሻል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በምክክሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተግኝተዋል።

በመስከረም ቸርነት