በኮንትሮባንድ የገቡ ሁለት ኮንቴነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎች ተያዙ

ሰኔ 29/2014(ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል በኮንትሮባንድ የገቡ ሁለት ኮንቴይነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የገቡት ሁለት ኮንቴይነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አጠና ተራ እና አዲሱ ሰፈር ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች ነው፡፡
አዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው የሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ 3-90864 ኢት ተሳቢ ኮድ 3-25413 ኢት እና ኮድ 3-93363 ኢት ተሳቢ ኮድ 3-25690 ኢት የሆኑ 2 ሎቤድ ተሽከርካሪዎች ኮንቴይነሮቹን ጭነው ጨለማን ተገን በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ/ም ከለሊቱ 8 ሰዓት ገደማ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል ተይዘዋል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡትን እና በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዕቃዎች ለቃሊቲ ጉምሩክ የማስረከብ ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሶ ጨለማን ተገን በማድረግ እና የሰዎች እንቅስቃሴ ጭር የሚልበትን አጋጣሚ በመጠበቅ ተመሳሳይ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከፀጥታ አካላት ክትትል እና ከህብረተሰቡ እይታ እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስቦ በከተማው ውስጥ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተባባሪነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡