በወላይታ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ሐምሌ 29/2016 (አዲስ ዋልታ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት ናዳ የ11 ሰዎች እንዲሁም በማንአራ ቀበሌ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።

ዛሬ ረፋድ 5 ሰዓት አካባቢ በጤፓ ቀበሌ በድጋሚ በተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

በወላይታ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የሕዝብ እና ሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክተር ዘለቀ ቦሎሎ በተከሰተው አደጋ እስካሁን በተደረገ ፍለጋ የ11 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን እና የአደጋው አስከፊነት እየጨመረ በመምጣቱ በአደጋው ቀጣና ያሉ ነዋሪዎችን የማዳን ሥራ መጀመሩን ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ገልጸዋል።

በተያያዘ በዞኑ ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ማንአራ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በአደጋው የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን በአንድ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰ ተገልጿል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ ዘለቀ ቦሎሎ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።