በወሎ ግንባር ህወሓት ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች መጠገን 

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) በወሎ ግንባር አሸባሪው ህወሓት ያወደማቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮችና ሰራዊቱ ለግዳጅ የሚንቀሳቀስባቸውን የገጠር መንገዶች በመጠገን ለህልውና ዘመቻው የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን የግንባሩ ዕዝ መሃንዲስ መምሪያ ኃላፊ ገለጹ።

መሃንዲስ መምሪያው ሰራዊቱ ለግዳጅ በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ ዘልቆ በመግባት ካለው የክረምት ወራት ጋር ተያይዞ በጎርፍ የተበላሹ መንገዶችን እየጠገነ ለተሽከርካሪ ምቹ በማድረግና ጠላት የሚፈጥራቸውን ሰው ሰራሽ መሰናክሎች በማስወገድ እየተመዘገበ ላለው ድል ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ክፍሉ በተቋሙ የቀረበለትን ዘመናዊ የምህንድስና ቁሳቁስ በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር በመቀየር የወገንን የሰው ሃይልና የታጠቃቸውን ከባድ መሳሪያዎች ድልድይ ፈጥሮ በማሻገር የአሸባሪው ቡድን ቅዥት ውጥን እውን አንዳይሆን ማድረጉን ኃላፊው አንስተዋል።

ለስራ በተንቀሳቀሱበት አካባቢ ሁሉ የማህበረሰቡ ድጋፍና እገዛ እንዳልተለያቸውም መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡