በውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ በትኩረት በመስራት የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር ይገባል

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) የምርምር ተቋማት በውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ በትኩረት በመስራት ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም እያካሄደ ነው።
በፎረሙ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የኅዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ባለሙያዎች ፣ የሌሎች ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ባለሙያዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎ እና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፎረሙ የውይይት የመነሻ ጥናታዊ ጹህፎች ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ፎረሙ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ከተፈጥሮ ከጸጋዎቿ እንዳትጠቀም ጫና ሲደረግባት መቆየቱን አንስተው፤ ይህም በልማቷ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ይህን ጫና በመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያኮራ ተግባር አከናውነዋል ብለዋል።

ለግድቡ ስኬት ርብርብ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት ምስጋና አቅርበው ፤ በቀጣይም በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ ጫና የሚያሳድሩ አካላትን ሃሳብ የማክሸፍ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ጊዜያት ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገራቸው ጥቅም መከበር እያደረጉት ያለው ትግል ከፍተኛ ድል እየተመዘገበበት እንደሚገኝም ገለጸዋል።

የተጀመረውን የጋራ ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ የፎረሙ ዋና ዓላማም “ምን ብናደርግ የኢትዮጵያን ጥቅም እናስከብራለን” በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም የምርምር ተቋማት በዲፕሎማሲ፣ በውሃ ልማትና ሚዲያ ዘርፉ ላይ በትኩረት በመስራት ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ውሃ ለኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መገለጫ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት ፍላጎቷን ለማረጋገጥ በቀጠናው ለሚገኙ እንደ ጅቡቲና ሱዳን ላሉ አገራት ያላትን በማካፈል እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከሌሎቹ የጎረቤት አገራት ጋር በትብብርና በጋራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።