በውጭ ሀገራት እየኖሩ የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከኢንተር ፖል ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራ የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

በውጭ ሀገራት እየኖሩ ከጁንታው ጋር ተባባሪ በመሆናቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራ የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።

በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ ዛሬ በመቐለ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የክልሉ ነዋሪ ህዝባዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለጹት።

ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በቁጥጥር ስር የዋሉና በቅርበት ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ተፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ሁሉንም የጁንታው አባላትን ለመያዝ አሁንም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የፌዴራል ፖሊስ በክልሉ ከተሞች ተልዕኮ ወስዶ ወደ ስራ መግባቱንም ነው ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ያስታወቁት።

“በክልሉ መደበኛ የፖሊስ ሥራ ለማስጀመርም የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች መቀሌ ገብተዋል” ብለዋል።

መኮንኖቹ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከዚህ በፊት መመሪያን ብቻ አክብረው ሲሰሩ የነበሩ የክልሉ ፖሊስ አባላትን በህዝብ በማስገምገም መደበኛውን የፖሊስ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርጉ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው የጦር መሳሪያዎችን እየመለሱ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ፍተሻዎችን በማካሄድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል።