በዓለም አቀፍ ከባቢ ብክለት ሳቢያ በአመት 9 ሚሊየን ሰዎች ይሞታሉ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) ከሁሉም አይነት መንሰኤዎች በሚከሰት ዓለም አቀፍ ብክለት ሳቢያ በአመት 9 ሚሊየን ሰዎች እንደሚሞቱ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

ከእነዚህም መካከል 55 በመቶው ሞት የተመዘገበው ከከባድ እና ቀላል ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ከኢንዱስትሪዎች ከሚለቀቁ በካይ ጋዞች አማካይነት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በመኖሪያ ቤት ውስጥ ለማብሰያነት ከምንጠቀመው የኃይል አማራጭ እንዲሁም በሰዎችና እንስሳት አማካይነት የሚከሰት የውሃ ብክለትም ለተመዘገበው የሞት መጠን የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ሲጃራ የሚያጨሱና ከሲጃራ አጫሾች የሚወጣው ጭስ የሚደርሳቸው ሰዎችም በብክለት ሳቢያ በሚከሰት ሞት ውስጥ መካተታቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ሙሉ በሙሉ የኢንዱስትሪ ሀገር የሆነችው አሜሪካ በፈረንጆቹ 2019  በብክለት ሳቢያ  142 ሺሕ 883 ዜጎቿን በአመት የምታጣ ሲሆን በብክለት ሳቢያ ብዙ ዜጎቿን በማጣት በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ቻይናና ህንድ በዚሁ ብክለት ሳቢያ እስከ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎቻቸውን በአመት የሚያጡ ሲሆን ይህም ይህም ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን የላንሴት ፕላኔቴሪ ኸልዝ ጆርናል ጥናት አመላክቷል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ የአየር ብክለት ሳቢያ ዜጎቿን በሞት የምትነጠቅ  ስትሆን በስምንትኛ ደረጃ ላይም ተቀምጣለች፡፡

በዚሁ ሳቢያ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች የህክምና ማህደር ሲመዘገብ በሳንባ አሊያም በልብ ህመም ወዘተ እየተባለ የሚጠቀስ መሆኑንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

በነስረዲን ኑሩ