በዓላት በሰለም እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) የገና በዓል እና መጪው የጥምቀት በዓል እንዲሁም በሀገሪቱ የሚካሄዱ ሌሎች ሀገራዊ እና አህጉራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ አስፈላጊውን የፀጥታና ደህንነት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ።

ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን እያለ የመልካም ምኞት መልዕክቱን ያስተላልፋል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያው ያለውን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ ገምግሟል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እስከአሁን ባከናወናቸው ተግባራት ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሣሪያዎች እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን በግምገማው አረጋግጧል።

አሁንም ፀረ-ሰላም ኃይሎች በተለያየ መልኩ ተደራጅተው አደጋዎችን ለማድረስ እየሰሩ ያሉ መሆናቸውን በቀረበው መረጃ አረጋግጧል።

የገና በዓል እና መጪው የጥምቀት በዓል እንዲሁም በሀገራችን የሚካሄዱ ሌሎች ሀገራዊ እና አህጉራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ አስፈላጊውን የፀጥታና ደህንነት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።

ፀረ-ሰላም ኃይሎች በተለይ መጪውን የገና እና የጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች መካከል ግጭት ለማስነሳት አጀንዳ ቀርፀው በተለያዩ ሚዲየሞች እያሰራጩ መሆናቸውን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ባደረገው የፀጥታ ሁኔታ ግምገማ ደርሶበታል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከሕዝብና መንግስት የተጣለበትን አደራና ተልዕኮ በታላቅ ሀገራዊ ስሜትና ፍቅር በብቃት እየተወጣ በተሰሩ ኦፕሬሽኖች የተያዙ የጦር መሣሪዎችንና የተጠርጣሪዎችን የምርመራ ውጤት በቀጣይ ለኅብረተሰቡ ያሳውቃል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪውን እያቀረበ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆንላችሁ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከልብ ይመኛል።

በመጨረሻም መላው ሕዝባችን የፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚያደርሱትን ጥፋት በውል ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባና ሰላሙን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በፍጥነት ለጋራ ግብረ-ኃይሉ በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11፣ 251115-52-63-03፣ 251115-52-40-77፣ 251115-54-36-78 እና 251115-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ መስጠትና በአካባቢው ላለ የፀጥታ ኃይልም መረጃውን በአካል ማድረስ እንደሚቻል ያስታውቃል፡፡

ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
አዲስ አበባ