በዘርፉ የተጀመሩ ለውጦችን ለማሳካት ስነ-ምግባር የተላበሱ አመራሮችና ባለሙያዎችን መፍጠር እንደሚገባ ተገለፀ

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ለማሳካት ተገቢውን ስነ-ምግባር የተላበሱ አመራሮችና ባለሙያዎች መፍጠር እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ማንደፍሮ (ፒኤችዲ) ገለጹ፡፡
በስነ-ምግባር የታነፀና ሥራውን በታማኝነት የሚፈጽም አመራርና ባለሙያ ለመፍጠር በትኩረት ይሰራልም ብለዋል፡፡
የሚኒስቴሩ አገልግሎት አሰጣጥ መዳከም የሀገር መዳከም መሆኑን በመረዳት አመራሮችና ባለሙያዎች ተገቢውን ስነ-ምግባር የተላበሱ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የስነ-ምግባር መርሆዎችን በትክክል ተግባራዊ በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጥ ዓርዓያ የሆነ እና ሥርዓት ያለው ተቋም ለመገንባት እንደሚሰራም ሚኒስትር ደኤታው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
አመራሮችና ባለሙያዎች ይህንን ተረድተው በግልፀኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ፣ ከአድሎ፣ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
ሚኒስቴር ለአመራሮቹና ሠራተኞቹ በለውጥ አመራር፣ በተቋማዊ ስነ-ምግባር፣ በውሳኔ አሰጣጥ እና በተግባቦት ዙሪያ እየሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ሁለተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡