በዘንድሮው ክረምት የሚተከሉ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

ችግኞች

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በዘንድሮው ክረምት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚዘጋጀው 6 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለጎረቤት ሀገራት በተለየ የችግኝ ጣቢያና በጀት ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም ገልጿል።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ እንደገለጹት፣ የዘንድሮ የክረምት ችግኝ ተከላ “አረንጓዴነትን በጋራ” በሚል መሪ ቃል ይከናወናል።

ለክረምቱ የችግኝ ተከላ ከሚፈለገው 6 ቢሊየን ችግኝ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ መዘጋጀቱን ያመለከቱት አቶ ተፈራ፣ አሀዙ በቆላማ አካባቢ እየፈሉ ያሉና ለቆጠራ ያልደረሱ ችግኞች አለማካተቱን አስታውቀዋል።

መኖ፣ ቀርቃሃና የመሳሰሉት ችግኞች በችግኝ ጣቢያዎች እየፈሉ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አንድ ችግኝ ከላስቲኩ በላይ ያለው አካል ጠንካራ ካልሆነ፣ ለስላሳ ከሆነና ተተክሎ ነፋስ፣ ጸሃይና ብርሃን መቋቋም ካልቻለ በመርዘሙ ብቻ አይተከልም ብለዋል።

“ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱት ችግኞች የተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ እንጂ ለተከላ አለመድረሳቸውና በደቡብ ክልል ውስጥ ካሉት ችግኞች በስተቀር ሌሎች ለተከላ የሚደርሱት እስከ ሰኔ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው” መሆኑን ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ ቆይቷል ያሉት አቶ ተፈራ፣ የችግኞች የመድረስ ጊዜ ከአሥር ወር እስከ ስድስት ወር የሚቆይ በመሆኑ የባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጥታ ወደ ዝግጅት ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።