በዙሪክ ደ ሲቪያ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸነፉ

የካቲት 14/2014 (ዋልታ) ትላንት በስፔን በተካሄደው ዙሪክ ደ ሲቪያ ማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸነፉ።

በዚሁ የዓለም አትሌቲክስ ኢሊት ሌብል የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች ኢትዮጵያዊያኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከታትለው በመግባት ድል አስመዘግበዋል።

አትሌት መገርቱ ዓለሙ 2:18:51 በሆነ የግል ምርጥ ሰዓት ስታሸንፍ አትሌት መሰረት ጎላ በ2:20:50 ሰዓት 2ኛ፣ አትሌት ካላዩ ቸኮል 2:21:17 ሰዓት 3ኛ እና አትሌት ጫልቱ ጪምዴሳ 2:22:13 ሰዓት 4ኛ በመግባት ውድድሩን ጨርሰዋል።

በወንዶች ደግሞ አትሌት አስራር አብዱራህማን 2:04:43 በሆነ ሰዓት በመግባት ሲያሸንፍ አትሌት አደላድለው ማሞ በመጀመሪያ ውድድሩ 2:05:12 በሆነ ሰዓት በመግባት 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል።

በሌላ በኩል በጉዋዳላጃራ ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት በሱ ሳዶ 1፡09፡12 ሰዓት በመግባት አሸንፋለች።

በተያያዘ ዜና የሌቪን 5 ኪሎ ሜትር ሪከርድን አሻሽላ ከ48 ሰዓታት ባነሰ ቆይታ በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ተካፍላ ድል ያስመዘገበችው አትሌት ዳዊት ስዩም ስትሆን በ4፡04.35 በሆነ ጊዜ ውድድሯን በድል አድራጊነት እንዳጠናቅቀች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ጠቅሶ የዘገበው ኢቢሲ ነው።