በዛምቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ አሸነፉ

ነሃሴ 10/2013(ዋልታ) በዛምቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ ሃካይንዴ ሂቺሌማ አሸነፉ፡፡

የዛምቢያ ምርጫ ኮሚሽን  ጉዳዩን አስመክቶ ባወጣው መግለጫ÷ በሀገሪቱ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ  ምርጫ የተቃዋሚው መሪ ሃካይንዴ  ሂቺሌማ  ማሸነፋቸውን አረጋግጧል፡፡

ሂቺሌማ  የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉን  ከ1 ሚሊየን በላይ  በሆነ ድምፅ በማግኘት ነው ምርጫውን ያሸነፉት፡፡

የተቃዋሚ መሪው ማሸነፋቸውን ተከትሎም ደጋፊዎቻቸው በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ ጎዳናዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሉንጉም በበኩላቸው÷ ምርጫው ነፃ ፣  ፍትሃዊ  እና ተዓማኒ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምርጫ ጣቢያዎች የተገኙ አባሎቻችን  በምርጫ ሃላፊዎች  መዋከብ ደርሶባቸዋል፤ በዚህም  የምርጫው ድምጽ  ለመጭበርበር ተጋልጧል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ሂቺሌማ በምላሻቸው  በቀድሞው ፕሬዚዳንት የቀረቡ ትችቶችን ውድቅ በማድረግ  መሰል  አስተያየቶች   ከተሸናፊ አካል የሚጠበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሂቺሌማ ከዚህ ቀደም ከ6 ጊዜ በላይ ለዛምቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በዕጩነት መቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡