በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ቤት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከበረ

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ቤት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡
በዛሬው እለት የትምህርት ቤቱን የ25 ዓመታት ጉዞ የሚዘክር አውደ ርዕይ ለእይታ በቅቷል፡፡
የትምህርት ቤቱ ኃላፊ አብዱልአዚዝ ዲኖ (ፒኤችዲ) አውደ ርዕዩ የማስተማሪያ ቁሳቁስና የተማሪዎች ስራዎች ያካተተና የትምህርት ቤቱን ታሪክ፣ አሁናዊ ገጽታና የወደፊት ዕቅዱን የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ የብሮድካስትና ኅትመትና ተግባቦት ትምህርቶች የደረሱበትን ደረጃ እንዲሁም ለጋዜጠኝነት ሙያ ያበረከተው አስተዋጽኦ ይታይበታልም ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ በመንግስት፣ በግልና በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማፍራት ለዘርፉ ማደግ የበኩሉን ሚና መወጣቱንም አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት ተሰማርተው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉንም እንዲሁ፡፡
ትምህርት ቤቱ በ1989 ዓ.ም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጅማ በር በሚገኘው በቀድሞው የኢትዮጵያ ራዲዮ ግቢ ውስጥ እንደተመሰረተም ማስታወሳቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
አሁን ላይ በብሮድካስት ጋዜጠኝነት፣ በመልቲ ሚዲያ ጋዜጠኝነትና በሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ከሙኒኬሽን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጥናት በሦስተኛ ዲግሪ እያስተማረ ሲሆን ተጨማሪ የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት የስርዓተትምህርት ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡