በደሴ ከተማ የህወሃትን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 8 ግለሰቦች ተያዙ

ነሃሴ 18/2013 (ዋልታ) – በደሴ ከተማ አስተዳደር ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር በተከናወነ የቅንጅት ስራ ስምንት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋት ለመመከት በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያን አዳክሞ ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ በንጹሃን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው አሰቃቂ ግፍና በደል እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ ከመፈጸሙም ባለፈ የአርሶ አደር ቤት እያቃጠለ፤ እንሰሳትንም እየገደለ፤ የቻለውን እየዘረፈ ያልቻለውን ደግሞ እያወደመ ለህዝቡ ያለውን ጥላቻ በተግባር እያሳየ በመሆኑ አሸባሪውን ህወሃት ተረባርበን መቅበር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በዚህ ክትትል የተያዙት ስምንቱ ግለሰቦች የጥፋት ተልዕኮ ለመፈጸም የመጡ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት መሆናቸው መረጋገጡንም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የጀመረውን የአሰሳ ስራና ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ የሚያረገውን ያልተቆጠበ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብም የጀመረውን አንድነት በማጠናከር አሸባሪው ቡድን ተስፋ በመቁረጥ እያደረሰ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት በደል ማስቆምና ህዝቡን መታደግ ይኖርበታልም” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአሸባሪው ቡድን ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው ደሴ ከተማ በ9 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለተጠለሉ ከ100 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችም የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው ጨምረው አስታውቀዋል።