በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተከናወነ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተከናወነ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል መሃዲ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የረጅም ዘመናት ትስስርና የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው ለሁለቱ ሀገራት ልማታዊ ዕድገት በትብብር መስራቱን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳኡ ዴንግ በበኩላቸው እንደ ሃገር እንድንቆም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለችልን እና ዛሬም ድረስ ከጎናችን ያልተለየች በመሆኗ እንደ ሁለተኛ ሀገራችን ለምንመለከታት ኢትዮጵያ ትልቅ ክብር አለን።

በቀጠናው የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ከሚወጣው ሠላም የማረጋገጥ ተልዕኮ ባሻገር በዘርፈ ብዙ የልማት መስኮች ድጋፍ እያደረገልን ይገኛል ያሉት ምክትል ሚኒስትሩ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ያሳየው እንቅስቃሴና ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑንም አክለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ፒኤችዲ) ሃሳብ አመንጭነት በሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ለመተግበር የታቀደውና በደቡብ ሱዳን ጁባ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ለተሳተፉ የ15ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ አመራሮች ኢምባሲው ምስጋና አቅርቧል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የ15ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ አመራሮች፤ በኢጋድ የኢትዮጵያ ተወካዮች፣ ጀኔራል መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ድጋፍ ሰጪ ቡድን አመራሮች፣ በጁባ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት፣ የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ተካፋይ እንደነበሩ የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመለክታል።