በደቡብ ክልል 46 በመቶ የሚሆኑ መራጮች መመዝገባቸው ተገለጸ

አቶ እርስቱ ይርዳው

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል 46 በመቶ የሚሆኑ መራጮች መመዝገባቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡

በክልሉ ይመዘገባሉ ከተባሉ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን መራጮች መካከል ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በተለይም ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ በተሰራው ሥራ 35 በመቶ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ለመራጭነት የደረሱ ዜጎች በመራጭነት መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከሶስት ቀናት በፊት 10 በመቶ መራጮች ብቻ ተመዝግበው እንደነበር የገለጹት አቶ እርስቱ፣ ባለፉት ሶስት ቀናት በህዝቡ ዘንድ የታየው መነቃቃት በተቀሩት ጥቂት ቀናትም እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከደሬቴድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡