በዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የከተማዋን ፀጥታ እየጠበቁ ነው

ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – የዳንሻ ከተማ ጸጥታ  እንዲጠበቅ  የከተማዋ  ነዋሪዎች  ከጸጥታ  አካላትና  አመራሮች  ጋር በቅንጅት  እየሰሩ መሆኑን  የከተማዋ  ከንቲባ  አቶ  ስልጣን  አድማሱ ገለፁ።

ከወራት በፊት በከተማዋ  በቅርበት  ላይ በሚገኘው 5ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር ላይ  ጥቃት  ያደረሰው  አሸባሪዉ ህወሃት  የከተማዋን የመንግስት  አገልግሎት የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት  ላይ  ጥቃት ማድረሱን ከንቲባው አስታዉሰው ተመሳሳይ  ጥቃት  እንዳይደርስ  የከተማው  ነዋሪዎች  በፈረቃ  አካባቢያቸውን እጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ከነዋሪው  በተጨማሪም  የክልል  እና  የፌደራል  የጸጥታ  አካላትም አካባቢውን በንቃት  እንደሚጠብቁ ከንቲባው አክለዋል።

በከተማዋ የትምህርት  ተቋማት  እንዳልተዘጉ የገለፁት  ከንቲባው  ባለፈው  አመት  ኮቪድን ያስከተለውን የትምህርት መስተጓጐል ትምህርት ቤቶች አካክሰዋል ብለዋል።

በከተማዋ ዙሪያው የሚከናወኑ የግብርና  ስራዎች  እንዳይስተጓጎሉ እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባው አክለዋል፡፡ የዘማች  አርሶ አደሮች  ማሳ ጾም  እንዳያድር  በአካባቢው ህብረተሰብ በትብብር  እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል።

(በታሪኳ መንግስተአብ)