በድሬዳዋ ለተደራጁ ወጣቶች አምስት ትራክተሮች ድጋፍ ተደረገ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በገጠር ቀበሌዎች በማህበር ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች በ5.2 ሚሊየን ብር የተገዙ የእርሻ ትራክተሮችን በድጋፍ አበረከተ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በአስተዳደሩ የተገዙ አምስት የእርሻ ትራክተሮችን ቁልፍ ለወጣቶቹ አበርክተዋል፡፡

ትራክተሮቹ በድጋፍ የተበረከቱት በአምስት ገጠር ቀበሌዎች ከ80 በላይ አባላት ላሏቸው አምስት የወጣት ማህበራት ነው።

የቢሮ ሀላፊው በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የህብረተሰቡን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ትራክተሮቹ የአርሶ አደሩን ማሳ በአነስተኛ ክፍያ በፍጥነትና በዘመናዊ መንገድ በማረስ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚያግዙ የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹም የተገኘውን የሥራ እድል በመጠቀም እና ጠንክሮ በመስራት ለሌሎች ምሳሌ እንሆናለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡