በድሬዳዋ ሰራዊቱን ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ሽኝት ተደረገ

ነሃሴ 18/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ለህልውና ዘመቻ የሃገር ጥሪን በመቀበል መከላከያ ሰራዊትን ለሚቀላቀሉ ተመላሽ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ሽኝት ተደረገላቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ መሃመድ ቡህ ከአባቶቻችን የተረከብናት ሃገር በህወሓት ሽብርተኛ ቡድን እንድትፈርስ ፈጽሞ አንፈቅድም ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን አደብ ለማስገዛትና ሃገርን ለትውልድ ከነ ሙሉ ክብሯ ለማስተላለፍ ዳግም ለሃገራዊ ግዳጅ በመዝመታችሁ አስተዳደሩ  ታላቅ አክብሮት አለው፤ በታሪክም ሲታወስ ይኖራል ነው ያሉት፡፡

የአስተዳደሩ ፍትህ ጸጥታና ህግ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ ጣሀ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከውስጥ እና ከውጭ የተደቀናበትን ጠላትና ችግር አሸንፋ እንድትወጣ ልጆቿ ድሬደዋን ጨምሮ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል የህልውና ዘመቻውን መቀላቀላቸውን አንስተዋል፡፡

ተመላሽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ግንባር በማቅናት በድል የሃገራችሁን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንደምታደርጉ ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

በሽኝት መርሃ ግብሩ የአሰተዳደሩ ከንቲባ ለተመላሽ የሰራዊት አባላት የሃገርን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ማስረከባቸውን ከድሬዳዋ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡