በድሬዳዋ አስተዳደር የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ የወባ በሽታን ለመከላከል ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም ከሀምሌ እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 987 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው ተገልጿል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል ከግሎባል ፈንድ በድጋፍ የተገኘው 287 ሺህ 732 የሚሆን አጎበር በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማና በገጠር ለሚገኙ ነዋሪዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚከፋፈል ተናግረዋል።
እንዲሁም ህብረተሰቡ አጎበርን የመጠቀም ልምዱ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ለህብረተሰቡ ስለ ወባ በሽታ አስከፊነት እንዲሁም የአጎበርን አጠቃቀም በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪውም አካባቢውን ከማፅዳት አንስቶ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም የወባ በሽታ ስርጭትን መከላከል እንደሚገባው መናገራቸውን ከከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡