በድሬዳዋ የህዝብና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሊደረግ  ነው

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም የህዝብና የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከሚያዝያ 1 ቀን ጀምሮ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

በዚህም በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠምና ጠቀሜታው ላይ ያተኮረ ስልጠና ለህዝብ እና ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች እንዲሁም ለትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና የትራፊክ አባላት መስጠቱ ተገልጿል።

በስልጠናው ላይ በተያዘው ወር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ በርካቶች ለህልፈት እንዲሁም ለአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ሰለባ በመሆን ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡

በትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ ለትራፊክ አደጋዎች በመንስኤነት ከተለዩት መካከል አንዱና ዋነኛው ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን  ወደ ትግበራ ለማስገባት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከሚደረገው የማስተማርና ማስገንዘብ ስራ በተጓዳኝ መሰል ህጎች እንዲከበሩ ተሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ የቁጥጥር ስርአቱ ይጠናከራል ብለዋል።

ለዚህም ከሚያዚያ አንድ ጀምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያን እንዲያስር ህጉን በማስከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ይሰራል ማለታቸውን ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።