በጉራ ፈርዳ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) በቀድሞው ደቡብ ክልል በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ 45 ተከሳሾች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሚዛን -ቦንጋ-ጋምቤላ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ሲሆን ተከሳሾች ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም ባሉ ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በወረዳው በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ጥቃት መሰንዘሩን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል፡፡

የሸኮና የመዠንገር ብሔረሰብ አባላት በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የጦር መሳሪያ አንስተው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ለማድረግ በማሰብ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጉራ ፈረዳ ወረዳ ጌኒቃ ቀበሌ ሌንጣ መንደር አንድ የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጅ ተገድሎ መገኘቱን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት መቀስቀሱን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ጠቅሷል፡፡

የሟች ገዳይ ማን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ ልጃችንን የገደሉት አማራዎች ናቸው በማለት የ30 ሰዎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አንዲጠፋ፣ 14 ሰዎች አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ ከሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም እና 5 ሺሕ 273 ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ፍርደኞቹ ጥቃት ማድረሳቸውም ተጠቅሷል፡፡

ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ወንጀሉ በተፈፀመበት ቦታ በመገኘት ምርመራ አድርጎ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሚዛን -ቦንጋ-ጋምቤላ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን ሲመለከተው ከቆየ በኋላ በ45 ተከሳሾች ላይ እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው ከሦስት ዓመት እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።