ሚያዝያ 1/2015 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በመንግስት የተጠናው የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ተግባራዊ ስራ መጀመሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር የልዩ ኃይል አደረጃጀቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በመንግስት የተጠናውን አዲሱን የልዩ ኃይል አደረጃጀት ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጀምሯል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በሚፈልጉት የጸጥታ መዋቅር ለመደራጀት ምዝገባ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከክልልና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ የልዩ ኃይል አባላት ወደሚፈልጉት የፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት መዋቅሮች የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አደረጃጀቱ የጸጥታ መዋቅሩን ይበልጥ የሚያጠናክረው በመሆኑ የክልሉ መንግስት በሙሉ ልብ ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም መናገራቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።