በግብርና ዘርፍ ያገኘነውን ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመድገም ትልቅ ትልም አለን – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) በግብርና ዘርፍ ያገኘነውን ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመድገም ትልቅ ትልም አለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን በኦሮሚያ ክልል እና በሲሲኢሲሲ መካከል በተደረገ በገዳ የኢኮኖሚ ዞን የሉሜ ነፃ የንግድ ቀጠና ማልማት ስራ የመግባቢያ ስምምነት መርኃግብር ማስጀመራቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።

ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የገዳ ኢንዱስትሪ ዞን የሀገራችን እና የቀጠናችን አቅም በመግለጥ ርዕያችንን ለማሳካት የሚረዳ ቁልፍ ተቋም ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

የሉሜ ነፃ የንግድ ቀጣና በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ሆኖ በምስረታው ብሎም ተግባራዊ ስራ በሚጀምርበት ወቅት ከድሬዳዋ በመቀጠል ሁለተኛው ነፃ የንግድ ቀጣና ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህም ነጻ የንግድ ቀጣናው ለኢኮኖሚ እድገት እና ልማት እድሎችን ያሰፋል ሲሉ ገልጸዋል።

በግብርና የተገኘው ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የመድገምን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የፖሊሲ ድጋፍ ብሎም ለኢኮኖሚ ዞኑ ቀጣይ እንቅስቃሴ ጠንካራ የመሰረተ ልማት ስራ ሊከናወን እንደሚገባ አስምረውበታል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በስተምሥራቅ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም ኤክስፖርትን ለማሳደግ፣ የንግድ እና ሎጂስቲክስ ማዕከል የመመስረት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ፣ የኢንዱስትሪ የንግድ ኢንቨስትመንት እና የከተማ ልማት ስራዎችን የማበልፀግ አላማ ያነገበ መሆኑ ተገልጿል።