በጎንደር ከተማ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጥፋት ያደረሱ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑ ተገለጸ

ሚያዚያ 19/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በህይዎትና አካል ጉዳት እንዲሁም በዘረፋ የተሰማሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ምክር ቤት ገልጿል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ምክር ቤቱ መግለጫ ያወጣ ሲሆን በግጭቱ በምንም ሁኔታ የሁለቱን እምነት ተከታይ ማኅበረሰብን የማይወክል ጥፋት መፈጸሙን አስታውቋል።

ጥፋቱ የተፈፀመው በጥቂት ጽንፈኛና አክራሪ ግለሰቦች መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፣ የሁለቱን እምነት ተከታዮች ወደ ለየለት ግጭት ለማስገባት ሆን ተብሎ ለግጭት የማያበቃ ምክንያትን በመምዘዝ ጥፋት እንዲፈጠር የተቀነባበረና የተመራ ሴራ መሆኑንም ጠቁሟል።

በዚህ እኩይ ተግባር ከሁለቱም የእምነት ተከታዮች የህይዎትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት መቃጠልና ዘረፋ ያጋጠመ ሲሆን በደረሰው ጉዳት የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑንም ገልጿል፡፡

ጎንደርን ማቃጠል፣ መዝረፍና ማዋረድን ተልዕኮው ያደረገው ይህ እኩይ ተግባር፤ በፀጥታ መዋቅሩ፣ በሁለቱም የእምነት አባቶችና ወጣቶች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት የፈለጉት ጥፋት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉንም አንስቷል።

በተፈጠረው ችግር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ሙስሊሞች እንዲሁም በመስጂድ ውስጥ የተጠለሉ የክርስትና አማኞች እንደነበሩና ከጥቃት የዳኑ መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል መግለጫው።

ይህ ልምድ ደግሞ የዛሬ ሳይሆን ትናንትም የእምነት ተቋማትና አባቶች የችግር ጊዜ ታማኝ መሸሸጊያ (መጠለያ) ዋስትና መተማመኛ መሆናቸው ታውቆ ያደረ በመሆኑ አንደኛው በሌላኛው በእጅጉ የሚያምን አንድና ያው የሚባል የሕብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው ነው።

የተፈጠረውን ቃጠሎም ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት በከፍተኛ ርብርብ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን፤ አሁን አካባቢው ሙሉ በሙሉ ከፀጥታ መዋቅርና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በመተባበር የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር በሁሉም አካባቢ ስምሪትና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

በተመሳሳይም የጎንደርን ሰላም ለማናጋት ጠላት የሸረበው ሴራ በማኅበረሰቡ እና በጸጥታ ሀይሉ ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ገለጿል።

የቢሮው ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ግጭቱ የተፈጠረው የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚያመልኩባቸው አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ለሥርዓተ ቀብር የሚሆን ድንጋይ ለማንሳት በነበረው ሂደት ሀብቱ የኛ ነው በሚል መሆኑን ገልጸዋል።

በግለሰቦች የተነሳው አለመግባባት የተለየ ተልዕኮ በነበራቸው አካላት ሰፍቶ የቡድን መልክ በመያዝ የከተማዋን ጸጥታ ለማድፍረስ መሞከሩንም ኃላፊው ለአሚኮ አስረድተዋል፡፡

አጋጣሚውን በመጠቀም አካባቢው ወደ አለመረጋጋት እንዲገባ ቢሞክርም በሁለቱ እምነት ተከታይ ወጣቶች እና በፀጥታ ሀይሉ ጥረት ጉዳዩ ሳይሳካ መቅረቱን ነው የተናገሩት።

ጉዳዩን ለማረጋጋት የተቻለ ቢሆንም አሁንም ችግር ለመፍጠር የሚሞክር አካል ካለ የፀጥታ ሀይሉ ያለምህረት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን አስረድተዋል።