በጎንደር የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ውይይት እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ከፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የከተማዋን የውሃ ችግር ይቀርፋሉ ተብለው የታሰቡትን የአንገረብ እና የመገጭ እንዲሁም በ161ሚን የተገነባውን የቆላድባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩሩ በጉብኝታቸው የተመለከቷቸውን ክፍተቶች ያነሱ ሲሆን ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና የህብረተሰቡን የውሃ እጦት ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር መክረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ችግሩን ለመቅረፍ በአካባቢው በሚገኙ የውሃ ግድቦች ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በአንገረብ እና በመገጭ የንፀህ መጠጥ ውሃ ግድቦች የሚከናወኑ ተግባራትን በትኩረት እንደሚከታተል ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ከንቲባ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው ለበርካታ አመታት የከተማው ሕዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለእንግልት መዳረጉን ያነሱ ሲሆን አፋጣኝ እልባት መሰጠት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል ፡፡

አመለወርቅ መኳንንት (ከጎንደር)