በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ተመረቀ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዓባይ ኅብረ-ዝማሬ ምርቃት እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ጥናት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር እየተካሄደ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አገርን ለማስቀጠል መንግሥትን ማፅናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘመኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ እኛ ሌላ አዳኝ ወይም ችግር ፈቺን የምናማትርበት ሳይሆን የራስ አቅምን መጠቀም የሚገባበት ነው ያሉት አማካሪው ማመን የሚገባውም በፈጣሪና በራስ አቅም ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ዲፕሎማሲውም መከወን ያለበት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከወላይታ፣ ቦንጋና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ቀጥሎ 4ኛ ሆኖ ዛሬ በጎንደር እየተከፈተ ያለው ማዕከል ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የውጭ ጫና መመከት ያስችላል ብለዋል።

ማዕከሉ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ዲፕሎማት ነው በሚል መርህ እንደ ዓባይና ኅዳሴ ግድብ ያሉ አጀንዳዎችን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመራማሪና ሞጋቾችን ይፈጥራል ብለዋል አምባሳደሩ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን አስታውሰው ይህን ዕድል ተጠቅማ ያሏትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች መሸጥ በዚህም የእድገት ምሰሶዎች ማድረግ ላይ መስራት እንደሚጠበቅ መክረዋል።

የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፀጋዎችን ለይቶ ለመስራት፣ ዓለም ዐቀፍ ጫናዎችን ለማሸነፍና በዲፕሎማሲው መስክ ልቆ ለመውጣት እያደረጉ ያለው ትብብር ደካማ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሆኖም አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲዎች እየተጀመረ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ የሚያስመዘግበው ውጤት እየላቀ እንደሚሄድ ጠቋሚዎች እየታዩ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ የዚሁ አካል የሆነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ጥናት ማዕከል ለአገራቸው የሚሞግቱ ተማሪዎችና መምህራንን ለማፍራት ይተጋል ነው ያሉት።

በፋሲለደስ የባሕል ቡድን የተዘጋጀውና የዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ባለቤት ቴዎድሮስ ካሳሁን ፕሮዲውሰርነት ተዘጋጅቶ የተመረቀው የዓባይ ኅብረ ዝማሬም የዚሁ ዲፕሎማሲ አካል ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበባት ማዕከል ዋና ዳይሬክተሩ ገብረማሪያም ይርጋ የዝማሬው አዘጋጅ መሆናቸው ተገልጿል።

በመርኃግብሩ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችና የበጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ስንታየሁ አባተ (ከጎንደር)