በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ ነው


ሐምሌ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ያዘጋጀውን የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ዛሬ በስፍራው በመገኘት አስረክቧል።

የቢሮው ኃላፊ ካሰች ኤልያስ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ቢሮው 750 ሊትር የምግብ ዘይት፣ ለ100 ጨቅላ ሕፃናት የሚሆን የዱቄት ወተትና አልባሳት እንዲሁም የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እና ሌሎች ድጋፎችን አበርክቷል።

ቢሮው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ በስፍራው ባለሙያዎችን በመመደብ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በስፍራው ተገኝተው ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ተጎጂዎችንም አጽናንተዋል።

ለተጎጂዎች ከጊዜያዊ ሰብዓዊ እርዳታ ባለፈ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል የክልሉ መንግስት ግብር ኃይል በማቋቋም ተግባራዊ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይም የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።