በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁመት ላይ የተሳለቀችው ጋዜጠኛ ተቀጣች

ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) ኮርቴዝ የተባለች የጣሊያን ጋዜጠኛ በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ቁመት ላይ በማኅበራዊ ትስስር ገጿ በመሳለቋ የ5 ሺሕ 500 ዶላር ቅጣት ለጠቅላይ ሚኒስትሯ እንድትከፍል ፍርድ ቤት ወስኖባታል፡፡

ይህም የሆነው ኮርቴዝ በማኅበራዊ ትስስር ገጿ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯን በጣም አጭር እንደሆችና ለማየት ራሱ እንደምትቸገር በመጻፏ ነው፡፡ ይህንንም የተከሰሰችበት ፍርድ ቤት በሰውነት መሳለቅ እና ስም ማጥፋት ነው ሲል ፈርጆታል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሯ እና በጋዜጠኛዋ መካከል ለመጀመርያ ጊዜ ግጭት የተፈጠረው ከሶስት ዓመት በፊት ሜሎኒ ስልጣን ላይ ባልነበሩበት ወቅት ነበር፡፡ ጋዜጠኛዋ በትዊተር ገጿ ላይ የተቀነባበረ የሜሎኒን ፎቶ ለጥፋ የነበረ ሲሆን ሜሎኒ ህጋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ስታሳውቅ ኮርቴዝ ፎቶውን ከገጿ ላይ አንስታ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በሌላ ልጥፍ ሜሎኒ እንደማታስፈራትና የጣሊያን ሚዲያዎች የሜሎኒ ቁመት 1 ነጥብ 63 ሜትር መሆኑን ቢዘግቡም እሷ ግን 1 ነጥብ 2 ሜትር መሆኗን በመግለጽ በጣም ትንሽ እንደሆነች እና ልታያት እንኳን እንደምትቸገር ጠቅሳ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም መጀመርያ የለጠፈችውን ፎቶ በማንሳቷ በሱ ክስ ያልተመሰረተባት ሲሆን አስከትላ በለጠፈችው ልጥፍ እንድትቀጣ ወስኗል፡፡ ጋዜጠኛዋም ይህን ተከትሎ የጣሊያን መንግስት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ችግር አለበት ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯም ከቅጣቱ የምታገኘውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለበጎ አድራጎት እንደምታውለው ገልጻለች፡፡