በጦርነቱ ከተጎዱ የጤና ተቋማት ከ85 በመቶው በላይ አገልግሎት እየሰጡ ነው

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ሰባተኛው የጤና ክብካቤ፣ ጥራትና ደሕንነት ጉባኤ “ቀጣይነት ያለው የጤና አገልግሎት ጥራት እና መማማር ለጥራት ባህል ግንባታ” በሚል መርሕ ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ የመሰረተ ልማትና የግብዓት አቅርቦት እየተሟላላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ለተቋማቱ የግብዓት አቅርቦት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በጉባኤው እንደሀገር የጤና ስርዓቱን ለማዘመን እና የተሻለ ለማድረግ በሚያስፈልጉ መስኮች ላይ ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማውጣት የጤና ሴክተሩን በቴክኖሎጂና ግብአት ለማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ተጠያቂነትን በመዘርጋት ጭምር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ይህም የተገልጋይ እርካታን ለማምጣት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምና ጥራት አገልግሎት ኦፊሰር ንጋቱ ሻንበል በበኩላቸው ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ደረጃ በደረጃ በማሟላት ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን አሁንም የህክምና መሳሪያዎች እጥረት በመኖሩ ምክንያት የጤና ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡