በፃድቃን ገ/ትንሣይ የሚመራው የህወሓት ኃይል ተመታ

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) –  በአሸባሪው ቁንጮ ፃድቃን ገ/ትንሣይ የሚመራው የጠላት ኃይል በሰሜን ወሎ ግንባር በተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት መመታቱ ተገለጸ፡፡

ዓርሚ ሁለት የሚባልና በከሀዲው ሜጀር ጄነራል ዮኋንስ፣ በምክትሉ ከሀዲው ማዕሾ በየነ እና ከሀዲው ከበደ ፍቃዱ እንዲሁም በሜካናይዝድ አዛዡ ከሀዲው ኮሎኔል ገ/ስላሴ የተመራው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጠላት ሀይል ድባቅ መመታቱ ተገልጿል፡፡

በግንባሩ የተሰማሩ ሁለት ክፍለ ጦር አዛዦች እንደተናገሩት፣ መንግስት የተናጠል የተኩሥ አቁም እርምጃውን ካነሳ በኋላ ከበላይ በተሠጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ጋሸናን ዋና ማዕከል በማድረግ ከዋድላ እስከ ላሊበላ መስመር ላይ የነበረውን የአሸባሪውን ኃይል መደምሠሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጠላት በጀግኖቹ የሠራዊት አባላት፣ ልዩ ኃይል እንዲሁም የሚሊሻ አባላትና የአካባቢው አርሶ አደር ከበባ ውስጥ ሆኖ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

ይህ የተዳከመ የጠላት ኃይል በጋሸና፣ መቄት፣ ሙጃ፣ በንፋሥ መውጫ አካባቢዎች እየተመታና እየተበተነ ይገኛል ማለታቸውን ከኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በነዚህ አካባቢዎች በጠላት ላይ በተደረገ ጥቃት 3 ድሽቃ፣ 6 ሺህ የድሽቃ ጥይት፣ 87 የዕጅ ቦምብ፣ 229 ክላሽንኮቭ ነፍስ ወከፍ መሣሪያ፣ 5 ሺህ የክላሽ ጥይት፣ 1 የጦርሜዳ መነፅር ሲማረክ፣ በርካታ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል እና ጠላት ይጠቀምባቸው የነበሩ 2 መድፎች እንዲሁም አንድ ዙ 23 መደምሰስ መቻሉን ዋና አዛዦቹ ገልፀዋል ሲል የመከላከያ ሰራዊት ገልጿል፡፡