በፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ መሆኑ ተገለጸ


ጥቅምት 25/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የባንኩ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ የሕብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የቁጠባ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 19 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል።

የቁጠባ መጠኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱን የተናገሩት ምክትል ገዢው ሁሉን አቀፍ የቁጠባ ሥርዓት ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ሴቶችና አነስተኛና መካከለኛ የሕብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ ሌሎችም የቁጠባ ልምድ እንዲያዳብሩ ተደርጓል ብለዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን በተለያዩ አማራጮች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የቁጠባና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ተደርጓልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የዲጂታል ሥርዓቱ መስፋፋት፣ የአዳዲስ ባንኮች ወደ ስራ መግባት፣ የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የመግባት እድል ተዳምረው ለቁጠባ ማደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።