ቢሮው ዲያስፖራዎችን ለማስተናገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገልጿል፡፡
የፌደራል ዲያስፖራ ጉዳዮች አገልግሎት እና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከስልጤ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር በ”ከኢድ እስከ ኢድ” ማዕቀፍ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በ”ከኢድ እስከ ኢድ” መርኃ ግብር መሰረት ወደ አገር ቤት የገቡ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ወራቤ ከተማ አቅንተዋል።
የስልጤ ዞን አስተዳዳሪ አሊ ከድር መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዲያስፖራው ማኀበረሰብ በሀገር እድገትና ልማት ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ስለመሆኑ አንስተዋል።
በክልል ደረጃ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እንደ ወሳኝ የእድገት አቅጣጫ ተይዞ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሀልገዮ ጂሎ ናቸው፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ዲያስፖራዎችን ለማስተናገድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እያደገ የመጣውን የዲያስፖራ ኢንቨስተር ለማስተናገድ ክልሉ ባሳየው ቁርጠኝነት በቢሊዮን ብር የሚገመት ካፒታል ያስመዘገቡ የዲያስፖራ አባላት ወደ ስራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ ስለመሆናቸውም ተጠቁሟል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት በክልሉና በስልጤ ዞን ስላሉ የኢንቨስትመት አማራጮችን ገለጻ የተደረገ ሲሆን አባላቱም በፈለጉት ዘርፍ በመሰማራት ለወገንና ለሀገር እድገት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
“አረፋን በደቡብ” በሚል መሪ ቃል በወራቤ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉት የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ከስልጤ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሆነው ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።