የካቲት 16/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለአራት ሬዲዮ ብሮድካስት ባለፈቃድ የኤፍኤም ጣቢያዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።
የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የኤፍኤም ጣቢያዎች መደበኛ ሥርጭት ባለመጀመራቸው፣ የሬድዮ ፈቃዱን ካገኙ ጀምሮ ሙዚቃ ብቻ በማጫወት በውድድር ፈቃድ ከወሰዱበት ውል ውጪ እየሰሩ እና ውስን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለብክነት እየዳረጉ በመሆኑ ማስጠንቀቂያውን መስጠቱን ባለስልጣኑ አመልክቷል።
የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የኤፍኤም ጣቢያዎችም ሟርሴ መልቲሚዲያ ኃ.የተ.የግ.ማ.(ጄ ሬዲዮ ጣቢያ 106.7 )፣ አዲስ ኦንላይን የግንኙነትና የግብይት ሥራ ኃ.የተ.የግ.ማ.(ሀበሻ ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ 98.7)፣ ትርታ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ. (ትርታ ሬዲዮ 97.6) እና ኢትዮ ዋርካ መልቲ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አ.ማ (ዋርካ ሬዲዮ 104.1) ናቸው።
እንደ የባለሥልጣኑ መግለጫ በውድድር የሚገኝን ይህን ውድ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት ለተፈቀደው እና ውል ለተገባበት ዓላማ እንዲውል በባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ቢሆንም በድርጅቶቹ በኩል የተለወጠ ነገር የለም።
ስለዚህም ሬድዮ ጣቢያዎቹ እስከ መጋቢት 01/2014 ዓ.ም ድረስ ውል በገቡት መሰረት መደበኛ ሥርጭታቸውን ካልጀመሩ ፈቃዳቸው በቀጥታ እንደሚሰረዝ አስታውቋል።
ጣቢያዎቹ መደበኛ ሥርጭቱን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ካልጀመሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት እጅግ ውስን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ጨረታ አውጥቶ በማወዳደር ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም እንደሚያውል አሳውቋል።