ባለሥልጣኑ በ1.9 ቢልዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን 14 የመንገድ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ

የካቲት 27/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በ1.9 ቢልዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን 14 የመንገድ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ፡፡

ባለሥልጣኑ በዛሬው ዕለት ግንባታቸው የተጠናቀቀ 14 የመንገድ ፕሮጀክቶችን በይፋ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

በምርቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመንገዶች መጠናቀቅ በመዲናዋ እያጋጠመ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያቃልል እና የትራፊክ አደጋንም የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ አያይዘውም ለሁሉም የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና በማቅረብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 9 መንገዶች፣ 2 የመኪና ማቆሚያዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች እንዲሁም የእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት የአስተዳደር ህንፃ ይገኙበታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የእግረኛ መንገዶችንና የመኪና ማቆሚያዎችን ሳይጨምር 19 ነጥብ 12 ኪ.ሜ ርዝመት እና ከ13 እስከ 60 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ 7 የሚሆኑት በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የተገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በተለያዩ የሥራ ተቋራጮች የተገነቡ መሆናቸውን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሞገስ ጥበቡ ገልፀዋል፡፡

የተመረቁት መንገዶች በመዲናዋ ያለውን የመንገድ ተደራሽነት በማሳደግ የተሻለ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ እና የመዲናዋን ገፅታ በመቀየር ረገድ የጎላ ሚና እንሚኖራቸውም አክለዋል፡፡

በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልቃድር፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የክፍለ ከተማና እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው የመንገድ ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

በአመለወረቅ መኳንንት