ባለስልጣኑ 3 ሺሕ 600 ተቋማት ላይ እርምጃ ወሰደ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን 3 ሺሕ 600 ነባር ማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ አገልግሎት መስጫ እና ችርቻሮ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

የፋሲካ በዓል እና የረመዳን የፆም ወቅትን ምክንያት በማድረግ ኅብረተሰቡ ለጤና ነክ ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ተቋሙ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

በዚህም የተለየ ጥቅም ለማግኘት ምግብ ላይ ባዕድ ነገር መጨመር እና የምግብ መከለስ እየተስተዋለ መሆኑ ተገልጿል።

ከምግብ ማጓጓዝ ጋር ተያይዞ በጥራት ባለማጓጓዝ ምክንያት ምግቦች እንዲመረዙ እና ለተለያዩ ኬሚካሎች እንዲጋለጡ በማድረግ በኅብረተሰቡ ላይ የጤና ጠንቅ እያስከተሉ ነው ተብሏል፡፡

ከበዓላት ጋር ተያይዞ ህገወጥ እርድ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተቋሙ ማረጋገጡን ገልጿል።

በመሆኑም ተቋሙ በ26 ሺሕ 843 ነባር ምግብ ማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ አገልግሎት መስጫ እና ችርቻሮ ተቋማት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጉድለት በተገኘባቸው 3 ሺሕ 600 የምግብ አምራች ተቋማት ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡

በዚህም 3 ሺሕ 291 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፣ 195 ብቃት ማረጋገጫ የታገዱ፣ 6 በህግ የተጠየቁ ሲሆን 133 በገንዘብ መቀጮ የተቀጡ ናቸው ተብሏል።

በተጨማሪም ግምታዊ ዋጋቸው 106 ሺሕ 609 የሆኑ 9 ሺሕ 54 ቁሳቁስ ደግሞ እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡

በሜሮን መስፍን