ባለስልጣኑ በ699 የጤና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ባካሄደው የተቋማት ደረጃ ልየታ በ699 የጤና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ በከተማዋ በሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ ባካሄደው የተቀናጀ ቁጥጥር የተገኙ ዋና ዋና ጉድለቶችና የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አምደየሱስ አድነው የልየታ ስራው ትኩረት በከተማዋ በጤና ቁጥጥር ዘርፍ ያለውን ብልሹ አሰራር በመለየት እና የእርምት እርምጃ በመውሰድ ለህብረተሰቡ ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎትና የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከማከዕል እስከ ወረዳ የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት ከሀገር አቀፍ ስታንዳርድ አንፃር ተቋማትን እንደየደረጃቸው ክትትልና ቁጥጥር ለማካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አጠቃላይ የታዩት 2 ሺሕ 537 ተቋማት ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ በተቀመጠው ቼክሊስቱ መሰረት ከ50 በታች ያመጡና በቀይ ደረጃ የተቀመጡ 77 ተቋማት፣ ከ50-75 በቢጫ ደረጃ የተቀመጡ 874፣ ከ75 በላይ ያስመዘገቡ እና በአረንጓዴ ደረጃ የተቀመጡ 1 ሺሕ 586 ተቋማት መሆናቸውን አስገንዝበዋል ፡፡
በዘመቻ ስራው ላይ የአሰራር ችግር ከታየባቸው ውስጥ ማስጠንቃቂያ የተሰጣቸው 84፣ የ3 ወር ጊዜ ማስጠንቃቂያ የተሰጣቸው 473፣ ውስን አገልግሎት የታገደባቸው 34፣ ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የታገዱ 108 በድምሩ 699 ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡
ከታዩት ጉድለቶች ውስጥ በአስተኝቶ ማከሚያ ክፍል መድኃኒት ቤት ያለመኖር፣ የፍሪጅ ቅዝቃዜን ሁኔታ በመመዝገብ አለመከታተል እና ማቀዝቀዣ ውስጥ ከመድሃኒት ጋር ምግብ ማስቀመጥ፣ መድሃኒት የተገዛበት ደረሰኝና የድንገተኛ መድሀኒቶች መመዝገቢያ መዝገብ አለመኖር ተጠቃሽ ናቸው።
የአገልግሎት ጊዜ ያለፈበት መድሃኒት መያዝ፣ ባለሙያ ያልሆነ ሰው ሲሰራ መገኘትና ከሙያ ዘርፍ ውጪ ሌላ ሰው መድቦ ማሰራት ከስነ ህንፃ፣ ከሙያዊ ትግበራ፣ ከግብዓትና ከባለሙያ አንፃር የተገኙ ዋና ዋና ጉድለቶች መሆናቸውንም ም/ዳይሬክተሩ መናገራቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።