ባለስልጣኑ ከ2 ሺሕ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ ከ2 ሺሕ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ይህንን ያስታወቀው የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ክንውንን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የባለስልጣኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋሁን አሉላ እንዳብራሩት በበጀት ዓመቱ በተለይም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባልተወጡ የሥራ ኃላፊዎችና ኦፊሰሮች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በዚህም ከ2 ሺሕ በላይ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ከሥራ ከገበታ ከማገድ ጀምሮ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም 14 ሠራተኞችና አመራሮች ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን አምስት ሠራተኞችና አመራሮች ደግሞ ከሥራ ገበታቸው እንዲባረሩ መደረጉን ነው የጠቆሙት።

ከ140 በላይ ሠራተኞችና አመራሮች ከባድ የዲሲፕሊን እርምጃ እንደተወሰደባቸው የገለጹት ሃላፊው፤ 1 ሺህ 842 የሚሆኑት ላይ ደግሞ ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት እንደተጣለባቸው ጠቅሰዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንዳሉት ባለስልጣኑ ደንብን በማስከበር በኩል የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመፍታት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡

የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከመሬት ወረራ፤ጎዳና ላይ ንግድ ፤ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና ከሌሎችም ህገ ወጥ ስራዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ደንብ የተላለፉ አካላት በስፋት የተስተዋሉበት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ይህን ህገ ወጥ ድርጊት ለመፍታት ባለስልጣኑ ከፀጥታ አካላት፣ከፍትህ ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሰራው ቅንጅታዊ ስራ በህገ ወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም ይህንን ቅንጅታዊ ስራ በማጠናከርና በዘርፉ የሚስተዋሉ የህግ ጥሰቶችን፣ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን በመከላከል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩም መናራቸውብ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተለያዩ ክፍለ ከተማ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የነበሩ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ ስራ ለመከወን መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡