ባለፉት ሦሥት ዓመታት የዳኞች ነፃነት እንዲኖር መሰራቱ ተገለፀ

ጥር 9/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ባለፉት ሦሥት ዓመታት የዳኞች ነፃነት እንዲኖር መሰራቱን ገለፁ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት «ፍርድ ቤት እና የሽግግር ፍትሕ በግጭት ጊዜ ወይም ከግጭት በኋላ» በሚል ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ባደረጉት ንግግር ሕዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ አመኔታ እያገኘ መምጣቱን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አንስተዋል፡፡
የዘገዩ መዝገቦችን የማጥራት ሥራ መሠራቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች ጫና ማሳረፉንም አመልክተዋል፡፡
ውይይቱ ግጭቶች ሲከሰቱ እና ከግጭት በኋላ አገራዊና ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸው ሚና፣ የሽግግር ፍትሕ፣ አገራዊና ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት ያደረሱ ጥፋተኞች ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በውይይቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና በቅርቡ ወደ አገራቸው የገቡ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ተስፋዬ አባተ