ነሀሴ 06/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ሳምንታት የኮቪድ- 19 ስርጭት አሳሳቢ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታና የክትባት ሂደቱን በተመለከተ የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው ባለፉት ሶስት ሳምንታት የወረርሽኙ ስርጭት አሳሳቢ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በሶስት ሳምንታት ውስጥ ናሙና ከሰጡ ሰዎች መካከል ኮቪድ-19 የተገኘባቸው በሳምንታዊ ምጣኔ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ወደ 7 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በሽታው የሚገኝባቸው ሰዎች አማካይ ቁጥር በሳምንት ከ831 የአራት እጥፍ ጭማሪ በማሳየት ወደ 3 ሺህ 302 ከፍ ብሏል ነው ያሉት።
ወደ ህክምና ማዕከላት የሚገቡ ህሙማን ቁጥር መጨመሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በአሁኑ ወቅት 324 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
በአንፃሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የሚጠቀሙ ሰዎች ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል ነው ያሉት።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመጠቀም ምጣኔው አሁን ላይ በአዲስ አበባ 59 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች ደግሞ ወደ 20 በመቶ አሽቆልቁሏል ብለዋል።
በመሆኑም በሶስተኛው ዙር የወረርሽኙ ስርጭት በሌሎች አገራት ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት በኢትዮጵያ እንዲከሰት ሊያደርግ ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል ሚኒስትሯ።
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሁሉንም ህብረተሰብ የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ስራ መሰራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የኮቪድ-19 ክትባትን በሚመለከት እስካሁን ባለው ሂደት 2 ሚሊዮን 254 ሺህ 270 ዜጎች የመጀመሪያ ዙር እንዲሁም ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ሁለተኛውን ዙር ክትባት አግኝተዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ካለው ከፍተኛ የወረርሽኙ ስርጭት አንፃር ክትባት ላልወሰዱ እድሜያቸው ከ35 አመት በላይ ለሆኑና በሌሎች ክልሎች ደግሞ እድሜያቸው ከ55 አመት በላይ ለሆኑ ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ ለሆኑ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ዜጎች ይሰጣልም ነው ያሉት።
የስራ ባህሪያቸው ከበርካታ ሰዎች ጋር ለሚያገናኛቸው ሰራተኞችም እንዲሁ ክትባቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ ከነገ ነሃሴ 7 ጀምሮ በክልሎች ደግሞ ከነሃሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ክትባቱ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎችም የጤና ቢሮዎች በሚያመቻቹት መርሃ ግብር መሰረት ክትባቱን ያገኛሉ ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።