ባለፉት አምስት ወራት ለትግራይ ክልል 269 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና ቁሳቁስ መላኩ ተገለጸ

የህክምና ቁሳቁስ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) ባለፉት አምስት ወራት ለትግራይ ክልል 269 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት መላኩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የጤና እና አልሚ ምግብ አቅርቦቶች፣ ፀረ-ካንሰር፣ የልብ ህክምና መድኃኒቶች፣ ART እና OI መድኃኒቶች፣ የቲቢ ህክምና መድኃኒቶች፣ የስኳር ህክምና መድኃኒቶች (ኢንሱሊን) እና ደም-ግፊት ህክምና መድኃኒቶች፣ አስፈላጊ አንቲባዮቲኮች እና ሌሎች አስፈላጊ መድኃኒቶች መላኩን አስታውቋል።

ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ለትግራይ ክልል ሕዝብ የሚያደርጉት የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ድጋፎች እንደቀጠሉ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ለትግራይ ሕዝብ ከጥር እስከ ግንቦት 2014 ዓ.ም አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች፣ ግብዓቶችን እና የሥነ-ምግብ አቅርቦቶችን በማመቻቸት እና በማድረስ በኩል በቅንጅት እና በቅርበት እየተሰራ ይገኛል ብሏል።

ባለፉት 5 ወራት የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል ወደ ትግራይ ክልል መላኩንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

እስካሁን እነዚህ ድጋፎች ቢደረጉም አሁንም ካለው ተጨማሪ ፍላጎት እና ከአይደር ሆስፒታል በቀረበው ጥያቄ መሰረት ጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መጋዘን በICRC እና በWHO በኩል የሚላኩ የማደንዘዣ መድኃኒቶችን ጨምሮ ተጨማሪ ጭነቶች መዘጋጀታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW